አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም – ወደፊት በመምጣት ላይ የሚገኘው አማራ ባንክ ለወዳጄ በተሰኘው አዲስ የዲጂታል ብድር አማካኝነት በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ቁጥራቸው ከ58ሺ በላይ ለሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባቀረበው አገልግሎት የሰጠው የብድር መጠን ከ1.05 ቢሊዮን ብር በላይ በማድረስ እጅግ አስደናቂ የሆነ ስኬት ማስመዝገቡን ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው የዲጂታል ብድር አገልግሎት መሰጠት ከጀመረ አራት ወራት ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ይህን ያህል የብድር መጠን ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ማቅረቡ ባንኩ ለዜጎች ህይወት መሻሻል እያበረከተ ያለውን አስተዋጽዖ ያሳያል፡፡
የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው “በለወዳጄ የዲጂታል ብድር አማካኝነት ከ1.05 ቢሊዮን ብር በላይ ማቅረብ መቻላችን ደንበኞቻችን በባንካችን ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነው። ይህ ቁጥር ከቁጥር በላይ ለባንካችን ትርጉም አለው፤ የፋይናንስ አቅም ማጎልበት መቻላችንን፣ የኢኮኖሚ ዕድል መፍጠራችንን እና በሺዎች የሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሕልማቸውን እንዲያሳኩ ማገዛችንን ያመለክታል። ይህንን የዲጂታል አገልግሎት አብዮት በመምራት፣ ደንበኞች ብድር በማግኘት ህይወታቸውን አንዲያሻሽሉ እድል በመፍጠራችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል፡፡
ለወዳጄ የዲጂታል ብድር አገልግሎት አማራ ባንክ ከክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ያቀረበው ሲሆን፣ አገልግሎቱ ፈጣን ለወዳጄና ደራሽ ለወዳጄ የተሰኙ የዲጂታል ብድር አይነቶች ተካተውበታል፡፡ በለወዳጄ የዲጂታል ብድር ተገልጋዮች ከ5ሺ እስከ 30 ሺህ ብር ድረስ ያለማስያዣ በንግድ ፈቃዳቸው ብቻ መበደር የሚችሉ ሲሆን የወሰዱትን ብድር በጊዜው እየከፈሉ የብድር አገልግሎቱን በዘላቂነት መጠቀም ይችላሉ፡፡
በመጨረሻም የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው “ገና ጅምር ላይ ነን፤ ራዕያችን የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የፋይናንስ ግቦች ለማሳካት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር ነው። ይህን ራዕይ እውን ለማድረግ ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት ማድረጋችንን፣ ፈጠራን ማበረታታችንንና ከአጋሮች ጋር መተባበራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
የለወዳጄ ብድር ተጠቃሚዎችን ምስክርነት የያዘ ቪዲዮ ይህን ማስፈንጠሪያ በመጫን ይመልከቱ – https://youtu.be/nSiNv3fGoQ0