አማራ ባንክ የ2024/25 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማና የ2025/26 በጀት ዓመታዊ የዕቅድ ውይይት የስራ አመራሮች ጉባዔ ሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ/ም ሲጠናቀቅ፣ የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የበጀት ዓመቱን ውጤታማ በሆነ ውጤት ያጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ውጤት ባንኩን ወደተሸለ ዕድገት ለማድረስ በተጀመረ ከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ የተገኘ መሆኑን አንስተዋል፡፡ አማራ ባንክ በቀጣይ 5 ዓመታት የላቀ አፈፃፀም ማስመዝገብ የሚያስችለውን ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ አጽድቆ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2030 በኢትዮጵያ ከሚገኙ ምርጥ 4 ባንኮች መካከለል አንዱ ለመሆንና እ.ኤ.አ በ2040 ከአፍሪካ ምርጥ 40 ባንኮች መካከል አንዱ ለመሆን ያስቀመጠውን ርዕይ ለማሳካት ደንበኛን ማዕከል ያደረገና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት በመስጠት፤ ተወዳዳሪ በመሆን ለሀገራችን ኢኮኖሚ የሚኖረውን ፋይዳ በማሳደግ የባአክሲዮኖችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ባንኩ በበጀት ዓመቱ ተደራሽነቱን ለማሳደግ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈትና የዲጅታል ባንክ አማራጮችን በመዘርጋት፣ የሰራተኞችን የመፈፀም አቅም በማሳደግና የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር፣ ወጪ ቆጣቢ የሆኑ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ ቁልፍ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ ዕቅዱን ለማሳካት ሁሉም የባንኩ ሰራተኛ ከተለመደው አሰራር በመውጣት በተለየ ትጋት፣ ቁርጠኝነት፣ በኃላፊነትና የቡድን መንፈስ በመስራት ባንኩን የሚመጥን አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡በመጨረሻም ዋና ስራ አስፈፃሚው ባንኩ በበጀት ዓመቱ ላስመዘገበው ውጤት አበርክቶ ለነበራቸው፣ ሁሉም ደንበኞች፣ የባንኩ ሰራተኞችና ባለአክሲዮኖች ምስጋናቸውን አቅርበው፤ በቀጣይም አማራ ባንክ በአዲስ ምዕራፍ፣ ወደ ላቀ ዕድገት ለሚያደርገው ጉዞ የተጠናከረ አብሮነታቸውንና አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠይቀዋል፡፡
አማራ ባንክ የ2024/25 በጀት ዓመት፤ የሥራ አፈፃጸም ጉባዔ ከሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
የአማራ ባንክ የ2024/25 በጀት ዓመት፤ የሥራ አፈፃጸም ጉባዔ ከሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ጉባዔው ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፤ የአማራ ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢና አባላት እንዲሁም ከፍተኛ የባንኩ አመራሮች፣ የዲስትሪክት እና የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡ በጉባዔው መክፈቻ፤ የአማራ ባንክ የዳይሬክሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ደበበ የበጀት ዓመቱ አፈፃፀምን ለመገምገም ለተገኙት ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የቦርድ ሰብሳቢው እንዳሉት ባንኩ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ገጥመውት ለነበሩት ተግዳሮቶች አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እንደተደረገና ዶ/ር ዮሐንስ አያሌውን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን ከሾመበት ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለውጡን የመሩበት መንገድ የሚያስደንቅ እና በበጀት ዓመቱ ለተመዘገበው ውጤት መሠረት የሆነ ነበር፡፡ ቦርዱ በተገባደደው በጀት ዓመት የባንኩን ለውጥ እና የወደፊት ዕድገትን ለመደገፍ ያስችል ዘንድ በርካታ ቁልፍ የሚባሉ ውሳኔዎችን እንዳስተላለፈ በተለይም ለረጅም ጊዜ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በማሻሻል ረገድ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሾሙ ቦርዱ ለባንኩ ሁለንተናዊ ዕድገት የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሳይ የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡ የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው ባንኩ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ገጥሞት የነበረውን ተግዳሮት ለመፍታት የባንኩ የዲይሬክተሮች ቦርድ ማስተዋል የተሞላበት ብልህ እርምጃ በመውሰድ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ አድርጎ ወደ ሥራ በማስገባቱ ባንኩ ወደ ስኬት በከፍተኛ እርምጃ መጓዝ እንዲጀምር አስችሎታል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዮሐንስ በሪፖርታቸው ይፋ እንዳደረጉት የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ብር 31.5 ቢሊዮን ማድረስ መቻሉ እና የደንበኞቹን ቁጥር ከ2.4 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም የቅርንጫፎቹን ቁጥር 316 ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ባንኩ በቅርቡ ባስተዋወቀው ለወዳጄ የዲጂታል አነስተኛ ብድር አገልግሎቱ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ከ97 ሺህ በላይ ለሆኑ ደንበኞች ብድር ያቀረበ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና በአነስተኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ዋነኞቹ ተጠቃሚዎች እንደነበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ አማራ ባንክ 70.8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማግኘት እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል 8.6 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደተቻለም አስታውቀዋል፡፡ በብድር አሰባሰብ ረገድ በዓመቱ 10.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ236.3 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ አማራ ባንክ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙና በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞቹ የሰጠው ጠቅላላ የብድር መጠን ከብር 26 ቢሊዮን በላይ ማድረሱንና የተበላሸ የብድር መጠኑ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ከፍተኛ ጣራ በታች መሆኑን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡ ይህ ውጤት የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ፣ የማኔጅመንት አባላትና ሁሉም የባንኩ ሠራተኞች በጋራ ባደረጉት ጥረት የተመዘገበ መሆኑን እውቅና በመስጠት፣ ሁሉም በየደረጃው ላበረከተው አስተዋጽዖ አመስግነው፤ አዲሱን የበጀት ዓመት በአዲስ ስትራቴጂ፣ ደንበኛ ተኮርና ቀልጣፋ አገልግሎት ስኬታማ ሆነን እንደምናጠናቅቅ ተስፋ አደርጋለሁ በማለት፤ ደንበኞችም አማራ ባንክ በያዘው የለውጥ አቅጣጫ ፍላጎታቸውን ያማከለ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አውቀው ከአማራ ባንክ ጋር አብረው እንዲሰሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አማራ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በበርካታ የባንክ የሥራ መለኪያዎች የተሻለ አፈፃጸም ማስመዝገቡ ተገለፀ፡፡
ባንኩ በተጠናቀቀው የ2024/25 በጀት ዓመት በበርካታ መለኪያዎች የተሻለ አፈፃጸም ማስመዝገቡን ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በዋና መ/ቤት በነበረ መርሃ ግብር አስታቋል፡፡ የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው በነበረው መርሃ ግብር እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በብድር እና የውጭ ምንዛሬ ስርጭት፣ በብድር አሰባሰብ እና በዲጅታል ባንኪንግ ትግበራ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ በዚህም መሠረት የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀ የ26 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፤ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የደንበኞቹን ቁጥር በ41 በመቶ በማሳደግ 2.4 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉም ነው የተገለፀው፡፡ በብድር አሰባሰብ ረገድ በዓመቱ 10.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ236.3 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፤ በሌላ በኩል በውጭ ምንዛሬ ግኝት ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር የ77.5 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በተያያዘም አማራ ባንክ በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ ያልተጣራ ትርፉን 1.1 ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻለ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ70 በመቶ ዕድገት የታየበት እንደሆነም ነው የተገለፀው፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር የ24.6 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 8.6 ቢሊዮን ብር ማድረስ የተቻለበት ውጤታማ አመት ማሳለፉን ባንኩ አስታውቋል። አማራ ባንክ ምንም እንኳ ከተመሠረተ ገና 3 ዓመት ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም ያለው አጠቃላይ ሀብት በ2024/25 በጀት ዓመት የ22 በመቶ ዕድገት በማሳየት 43.1 ቢሊዮን ብር ማድረሱም ነው የታወቀው፡፡ ይህንን የባንኩን ጥረት የተረዳው የአማራ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከማኔጅመንቱ የቀረበለትን አዲስ የደመወዝ ስኬል እና ጥቅማጥቅም ጥያቄ በዝርዝር ተመልክቶ ጥያቄው ተገቢና አስፈላጊ መሆኑን በማመን በሙሉ ድምጽ መፍቀዱም በዕለቱ በነበረው መርሃ ግብር ይፋ ተደርጓል፡፡ ባንኩ በቀጣይ የበጀት ዓመት በዋናነት በሃብት ማሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ የባንኩን የወደፊት ተወዳዳሪነት የሚያስቀጥሉ የዲጂታል ማስፋፋትና የደንበኞቻችንን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቋል። አማራ ባንክ ከባንክ ባሻገር!
አማራ ባንክ የ15ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ለሚገኘው ዓባይ ባንክ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላለፈ፡
(ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም) አማራ ባንክ ዓባይ ባንክ ሥራ የጀመረበትን የ15ኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ የመልካም ምኞት መልዕክቱን በዓባይ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚና ሌሎች ምክትል ሥራ አስፈፃሚዎች በተገኙበት ለባንኩ ያለውን መልካም ምኞት አስተላልፏል፡፡ ከአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የተላከውን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያደረሱት የአማራ ባንክ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አባላት እና የተለያዩ መምሪያ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ አማራ ባንክን በመወከል መልዕክትያስተላለፉት የአማራ ባንክ የህዝብ ግንኙነት እና ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ ሲሆኑ፣ ዓባይ ባንክ ባለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እዚህ ደረጃ የደረሰ ባንክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ የኋላ ገሠሠ አማራ ባንክ ላቀረበው የመልካም ምኞት እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ዓባይ ባንክ ከባንኩ ምስረታ ጀምሮ አብሮ እየሠራ መቆየቱን ጠቅሰው በቀጣይም የሁለቱ ባንኮች ግንኙነት በሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ አማራ ባንክከባንክ ባሻገር!
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው አማራ ባንክ የሚሰጣቸውን የፋይናንስ አገልግሎቶች ለጎብኝዎች አቀረበ።
የአማራ ባንክ የዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ እሸቴ የማታ የዲጂታል ባንክ ሽግግርን ለማፋጠን ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም አማራ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በቅርብ ዓመታት ዘርፉን የተቀላቀለ የፋይናንስ ተቋም እንደመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው እና ከ1200 በላይ የፋይናንስ ሴክተር ባለድርሻ አካላትን፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን፣ ተቆጣጣሪዎችን እና የሴት የፋይናንስ መሪዎችን ባሰባሰበው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም ላይ ተሳታፊ በመሆኑ ኩራት ይሰማዋል። በዚሁ ፎረም ላይ አማራ ባንክ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ንግዶችን ለመደገፍ እና በሀገራችን ያሉ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማብቃት ታስበው የተዘጋጁ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ መሆኑን የሚያሳዩ ስራዎችን ለእይታ አቅርቧል።የአማራ ባንክ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ የሆኑት አቶ እሸቴ የማታ እንዳሉት፥ “በኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም ላይ በመሳተፋችንና የፋይናንስ ዘርፉን ምህዳር የወደፊት ዕጣ በሚወስኑ ወሳኝ ዉይይቶች ላይ አስተዋፅዖ በማድረጋችን እጅግ ደስተኞች ነን። አማራ ባንክ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማስፋት፣ ስራ ፈጣሪዎችን ለማብቃት እና በመላ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን በቁርጠኝነት እየሰራ ያለ ባንክ ነው። የፋይናንስ ተደራሽነትንና ዘላቂ ልማትን ለማሳደግ ትልቅ የፈጠራና ትብብር እድል እንዳለ እናምናለን፤ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ እንደ ባለድርሻ አካል ያለብን ኃላፊነት እንደሆነ እናምናለን።”በተጨማሪም አማራ ባንክ የሚሰጣቸውን የባንክ አገልግሎቶች በፋይናንስ ጉባኤ ላይ ለተገኙ ተሳታፊዎች ከማቅረብ ባሻገር፣ አሁን ያሉ አገልግሎቶችን ይበልጥ ሊያሳድጉና ደንበኞቹን በተሻለ ሁኔታ ሊያገለግሉ የሚችሉ በፈጠራ የታገዙ አገልግሎቶችን ለመፈለግ ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለመስራት በንቃት እንደሚሳተፍ ተገልጿል።የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዘጋጅነት ግንቦት 7 እና 8 ቀን 2017 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።
አማራ ባንክ ለወዳጄ በተሰኘ የዲጂታል ብድር አማካኝነት ከ1.05 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በማቅረብ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አስታወቀ።
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም – ወደፊት በመምጣት ላይ የሚገኘው አማራ ባንክ ለወዳጄ በተሰኘው አዲስ የዲጂታል ብድር አማካኝነት በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ቁጥራቸው ከ58ሺ በላይ ለሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባቀረበው አገልግሎት የሰጠው የብድር መጠን ከ1.05 ቢሊዮን ብር በላይ በማድረስ እጅግ አስደናቂ የሆነ ስኬት ማስመዝገቡን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው የዲጂታል ብድር አገልግሎት መሰጠት ከጀመረ አራት ወራት ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ይህን ያህል የብድር መጠን ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ማቅረቡ ባንኩ ለዜጎች ህይወት መሻሻል እያበረከተ ያለውን አስተዋጽዖ ያሳያል፡፡ የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው “በለወዳጄ የዲጂታል ብድር አማካኝነት ከ1.05 ቢሊዮን ብር በላይ ማቅረብ መቻላችን ደንበኞቻችን በባንካችን ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነው። ይህ ቁጥር ከቁጥር በላይ ለባንካችን ትርጉም አለው፤ የፋይናንስ አቅም ማጎልበት መቻላችንን፣ የኢኮኖሚ ዕድል መፍጠራችንን እና በሺዎች የሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሕልማቸውን እንዲያሳኩ ማገዛችንን ያመለክታል። ይህንን የዲጂታል አገልግሎት አብዮት በመምራት፣ ደንበኞች ብድር በማግኘት ህይወታቸውን አንዲያሻሽሉ እድል በመፍጠራችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል፡፡ ለወዳጄ የዲጂታል ብድር አገልግሎት አማራ ባንክ ከክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ያቀረበው ሲሆን፣ አገልግሎቱ ፈጣን ለወዳጄና ደራሽ ለወዳጄ የተሰኙ የዲጂታል ብድር አይነቶች ተካተውበታል፡፡ በለወዳጄ የዲጂታል ብድር ተገልጋዮች ከ5ሺ እስከ 30 ሺህ ብር ድረስ ያለማስያዣ በንግድ ፈቃዳቸው ብቻ መበደር የሚችሉ ሲሆን የወሰዱትን ብድር በጊዜው እየከፈሉ የብድር አገልግሎቱን በዘላቂነት መጠቀም ይችላሉ፡፡ በመጨረሻም የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው “ገና ጅምር ላይ ነን፤ ራዕያችን የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የፋይናንስ ግቦች ለማሳካት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር ነው። ይህን ራዕይ እውን ለማድረግ ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት ማድረጋችንን፣ ፈጠራን ማበረታታችንንና ከአጋሮች ጋር መተባበራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡ የለወዳጄ ብድር ተጠቃሚዎችን ምስክርነት የያዘ ቪዲዮ ይህን ማስፈንጠሪያ በመጫን ይመልከቱ – https://youtu.be/nSiNv3fGoQ0
የባንካችን የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም ስብሰባ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
(ሚያዚያ 29፣ 2017 ዓ.ም) የአማራ ባንክ የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም ስብሰባ የባንኩ አመራር አባላትና፣ የዲስትሪክት እና የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች በተገኙበት በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ሲሆን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ስብሰባውን በመክፈቻ ንግግር አስጀምረዋል፡፡ አማራ ባንክከባንክ ባሻገር!
አማራ ባንክ የ1446ኛውን የረመዷን ጾም እና የዒድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፍ አደረገ!
(ሀሙስ መጋቢት 18 ቀን 2017) አማራ ባንክ የ1446ኛውን የረመዷን ፆም እና የዒድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፍ አደረገ! በመርሃ-ግብሩ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች በተለያዩ አካባቢዎች በመገኘት ለአቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የአማራ ባንክ መርሃባ – ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መምሪያ ተወካይ ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት ተስፋዬ በድጋፍ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ባንኩ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ የሸሪአ መርህን መሠረት ያደረገ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ባንኩ ከወለድ ነፃ አገልግሎት መስጠቱ በርካታ የአገራችንን ህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ ያስችላል ያሉት ወ/ሮ መሰረት፤ መርሃባ የአማራ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች እንዲሁም ለአገልግሎቱ በተለዩ 14 ቅርንጫፎች እየሰጠ በመሆኑ ገልጸዋል። አገልግሎቱ ካለው ፍላጎት አንጻር ሲታይ አሁንም ተካታች ያልሆነ የህብረተሰብ ክፍል ብዙ በመሆኑ፤ ህብረሰተቡ የሚፈልገውን አማራጭ በማቅረብ ማገልገል እንደሚገባና አማራ ባንክ የዋዲዓህ፣ አማና፣ ቀርድ እና የሙደረባህ ኢንቨስትመንት፣ እና ሌሎችንም አገልግሎቶች እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የመርሃባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ጋብዘዋል፡፡ አማራ ባንክ ከተመሰረተ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ የዒድ አልፈጥር በዓልን ጨምሮ የተለያዩ በዓላትን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ለአቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፍ እያካሄደ መሆኑም ተገልጿል፡፡አማራ ባንክ መጪው የዒድ አልፊጥር በዓል የሰላምና የደስታ እንዲሆን ይመኛል! አማራ ባንክከባንክ ባሻገር
አማራ ባንክ ከጉዛም ቴክኖሎጂስ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ።
(የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም) አማራ ባንክ በፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ዙሪያ እያካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል በማቀድ ከአለም አቀፍ የሥርዓት ዲዛይንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት (ጉዛም ቴክኖሎጂ) ጋር በአጋርነት ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ በዛሬው እለት ተፈራረመ። አማራ ባንክ ከጉዛም ጋር በቴክኖሎጂ መፍትሄዎች ዙሪያ ሰተራቴጂክ አጋርነት በመመስረት ራዕዩን እውን የሚደርግባቸውን ስራዎች ለመስራት መግባባት ላይ ደርሷል፡፡ ጉዛም ቴክኖሎጂ በአማራ ባንክ የሚታዩትን የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ቢዝነስ ክፍተቶችን በመለየት (Gap Analysis) በመስራት የተሻሉ የመፍትሄ አማራጮችን ማስቀመጥ ቀዳሚ ስራው ይሆናል፡፡ አማራ ባንክ ከባንክ ባሻገር!