አማራ ባንክ ከጳጉሜን 3 ቀን 2017 – ጥቅምት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ግብይታቸውን በፖስ እና ኪውአር ኮድ አማራጮች ያከናወኑ ዕድለኛ ደንበኞችን ሸልሟል፡፡ባንኩ በኪውአር እና ፖስ የሚደረጉ ግብይቶችን ለማሳደግ ለሁለት ወራት ገደማ አካሂዶት በነበረው በዚህ ዘመቻ 65 ዕድለኛ ደንበኞችን ኅዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም በብሔራዊ ሎተሪ በነበረ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች እና የብሔራዊ ሎተሪ ታዛቢዎች በተገኙበት ማካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ዕጣው የወጣላቸው ዕድለኞች ሽልማታቸውን ታኅሣሥ 10 ቀን 2018 ዓ.ም በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በነበረ ሥነ-ሥርዓት መረከብ ችለዋል፡፡ ሽልማቱም በዘመቻው ላይ መተገለፀው መሠረት ከብር 5 ሺህ ጀምሮ እስከ ብር 50 ሺህ ነበረ፡፡በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ባንክ የባንኪንግ ኦፕሬሽን ተ/ዋና መኮንን የሆኑት አቶ እሸቴ የማታ ለዕድለኞች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ዲጂታል ባንኪንግ ጊዜን በመቆጠብ እና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ገንዘብን በቀላሉ ማንቀሳቀስ የሚያስችል አማራጭ በመሆኑ ሁሉም ሊጠቀመው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ተሸላሚ ዕድለኞች በበኩላቸው ባንኩ ቃል በገባው መሠረት ሽልማቱን በወቅቱ በመስጠቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ባንኩ በዲጂታል ባንኪንግ ዘርፍ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡አማራ ባንክከባንክ ባሻገር!
አማራ ባንክና ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ የሰነደ መዋለ ንዋይ ምዝገባን በተመለከተ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ ታህሳስ 9 ቀን 2018 ዓ.ም አማራ ባንክ፣ ከወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት በወጋገን ካፒታል ዋና መስሪያ ቤት ተፈራረመ፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የአማራ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) እና የወጋገን ካፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይ. ብሩታዊት ዳዊት ናቸው፡፡ የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የህዝብ አክሲዮን ኩባንያዎች የመመዝገብ ግዴታ ባስቀመጠዉ መመሪያ መሰረት፤ አማራ ባንክ በባለአክሲዮኖቹ የተያዙትን ሰነደመዋለ ነዋዮች በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የማስመዝገብ ሂደቱን የደንበኛ ሳቢ መግለጫ (Prospectus) ማዘጋጀትን ጨምሮ እንዲያስተባብርና ሌሎች ከካፒታል ገበያ ጋር የተያያዙ የማማከር ስራዎችን እንዲሰራ ኃላፊነቱ ለወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ በሰጠው መሠረት አማራ ባንክ ለካፒታል ባንኩ አስፈላጊ መረጃዎችን ማቅረብ ችሏል ብለዋል፡፡ አማራ ባንክ የአክሲዮን ገበያ ባልነበረት ጊዜ ከ164,000 በላይ ባለአክሲዮኖችን እምነት በማግኘት የባንኩን አክሲዮኖች ለመሸጥ የቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዘመናዊና የተማከለ የካፒታል ገበያ አማካኝነት የመጡ ተጨማሪ እድሎችንን ለመጠቀምና በኢትዮጵያ እያደገ ባለው የካፒታል ገበያ ውስጥ ባንኩ በሚኖረው ንቁ ተሳትፎ ማለትም በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ላይ የባንኩን አክሲዮኖችን እንዲሸጥ ለማስቻል፣ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለማቋቋም፣ ተጨማሪ ካፒታል ማሰባሰብ የመሳሰሉ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሁለቱ ተቋማት የተፈራረሙት ስምምነቶች ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ገልጸዋል። የወጋገን ካፒታል ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይ. ብሩታዊት ዳዊት በበኩላቸው አማራ ባንክ በአገሪቱ የካፒታል ገበያ ውስጥ ለሚኖረው ሚናና ተሳትፎ ወጋገን ካፒታል ባንክ ላይ ኃላፊነትና እምነት ስለጣለ ያመሰገኑ ሲሆን፣ ኢንቨስትመንት ባንኩ የተሰጡትን ኃለፊነቶች በሚገባ እንደሚወጣ በማረጋገጥ ለአማራ ባንክ የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡ አማራ ባንክከባንክ ባሻገር!
የአማራ ባንክ በ2018 መጀመሪያ አምስት ወራት 1.15 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዘገበ።
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ ታህሳስ 03 ቀን 2018 ዓ.ም የአማራ ባንክ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ብቻ (ከሐምሌ 1 እስከ ህዳር 30 ቀን 2018) በዋና ዋና የፋይናንስ አፈጻጸም ቁልፍ የሥራ መስኮች ላይ ጠንካራና ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ ከታክስ በፊት የ1.15 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል። ይህ የላቀ ትርፍ የተገኘው በ2017 በጀት ዓመት ከተመዘገበው የ910.2 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አምስት ወራት 3.55 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስመዝገብ እንደተቻለ ዋና ስራ አስፈፃመሚው ጠቅሰዋል። ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም በእነዚህ አምስት ወራት ውስጥ የተመዘገበው አፈጻጸም ስትራቴጂካዊ ትኩረት በጠንካራ የሀብት ማሰባሰብ፣ በዲጅታል ትራንስፎርሜሽንና በብድር አስተዳደር ላይ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ላይ አተኩሮ መስራት በመቻላቸው የመጣ ነው ብለዋል። ቁልፍ የአፈጻጸም ዋና ዋና መረጃዎች፡- የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፡ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን እስከ ህዳር 2018 ዓ.ም 35.8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ዕድገቱ 82 በመቶ ሆኗል። ይህም በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ የ4.29 ቢሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል። የውጭ ምንዛሪ (FCY) አሰባሰብ፡- የአማራ ባንክ የ76.58 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ በመሰብሰብ የላቀ አፈጻጸም አሳይቷል፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ313 በመቶ ብልጫ አለው። የብድር አቅርቦትና የሀብት ጥራት፡- አማራ ባንክ ከተመሰረተ ጀምሮ ያቀረበው አጠቃላይ ብድርና የቅድሚያ ክፍያ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት በ53.8 በመቶ በማሳደግ ወደ 31.3 ቢሊዮን ብር አበድሯል። በብድር አሰባሰብ፡- በህዳር 2017 ከነበረበት 12.9 በመቶ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ያልተከፈለ/የተበላሸ/ ብድር (NPL) ጥምርታ በአስደናቂ ሁኔታ በማውረድ ወደ 4.06 በመቶ እንዲደርስ ርብርብ ተደርጓል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኅዳር 20 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው በባንኩ 4ኛ ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጉባኤ ላይ በከፍተኛ ጉጉት የተሰባሰበው ተሳታፊ ከጠዋቱ ጀምሮ ሲታይ አስደሳች ድባብ ፈጥሮ የነበረ ሲሆን በአስደናቂው ቀን ከጠዋቱ 3፡30 ላይ ዝቅተኛው የምልአተ ጉባኤ ገደብ መሟላት ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ መሻገር ችሎ ነበር። ይህም ባለአክሲዮኖች በአማራ ባንክ ራዕይ እና አመራር ላይ ያላቸውን ጥልቅ እምነትና ቁርጠኝነት ያሳያል። ለዚህምልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን። አማራ ባንክከባንክ ባሻገር!
አማራ ባንክ በዛሬው ዕለት ለአሸናፊ ደንበኞች የተዘጋጀውን የገንዘብ ሽልማት ዕጣ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት አከናወነ።
ባንካችን ላለፉት ሁለት ወራት ሲያከናውን የቆየውን በፖስ (POS) እና በኪው አር ኮድ (QR Code) አማራጮች ግብይት የሚያከናውኑ ደንበኞችን የሚያበረታታ ዘመቻ በይፋ በማጠናቀቅ በዛሬው ዕለት ለአሸናፊ ደንበኞች የተዘጋጀውን የገንዘብ ሽልማት ዕጣ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት አከናወነ። ዕጣ የማውጣቱ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ህዳር 26 ቀን 2018 ዓ.ም የባንካችን የዲጂታል ባንክ ተቀዳሚ ኦፊሰር የሆኑት አቶ በፍቃዱ ቸርነትና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶችና ታዛቢዎች በተገኙበት በኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት አዳራሽ ተካሂዷል። በወጣው ዕጣ መሰረትም 50 ሽህ ብር የሚያስገኘው ሶስት አሸናፊ የዕጣ ቁጥሮች FT25283HJHS6፤ FT252743MN3Z እና FT2526077BVP ሆኖ የወጣ ሲሆን ዕድለኞችም የባንካችን ፋሲሎ፤ ሰቆጣ እና መሪ ቅርንጫፍ ደንበኞች ሆነዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ከባንካች ደንበኞች ግንኙነት ማዕከል ውጪ ምንም አይነት የስልክ ጥሪ ምላሽ ባለመስጠት እንዲሁም ማንኛውም አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥማችሁ ወደ 690 የደንበኞች ግንኙነት ማዕከላችን በመደወል እራሳችሁን ከአጭበርባሪዎች እንድትጠብቁ እናሳስባለን፡፡ አማራ ባንክከባንክ ባሻገር!
አማራ ባንክ ጠቅላላ ሐብቱ 43.4 ቢሊዮን ብር ደረሰ።
የአማራ ባንክ ጠቅላላ ሀብት 43 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀ የ23.2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የአማራ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮሐንስ አያሌው (ፒኤችዲ) አስታወቁ።የአማራ ባንክ የባለአክስዮኖች 4ኛ ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሚሊኒየም አዳራሽ ከሰሞኑ ተካሂዷል።በጠቅላላ ጉባኤው ባለአክሲዮኖች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የማኔጅመንት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤትና የሚዲያ ተወካዮች በተገኙበት የባንኩ ዓመታዊ አፈጻጸምና ሌሎች የፋይናንስና ፋይናንስ ነክ ባልሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህ ወሳኝ ጉባኤ የባንኩ የቀጣይ ዓመታት ጉዞ ውይይት ተደርጎበታል።የዓለም ዓቀፍ የኢኮኖሚ መዋዠቅና በአገር ውስጥ በመንግስት በተካሄደው መዋቅራዊ ማስተካከያ በታየበት ዓመት አማራ ባንክ ልዩ ጥንካሬና ተወዳዳሪነት በማሳየቱ በ2017 በጀት ዓመት አመርቂ የፋይናንስ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ተገልጿል።በጉባኤው የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮሐንስ አያሌው (ፒኤችዲ) እንዳሉት፣ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 655 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ85 በመቶ ብልጫ ያለው ነው። የባንኩ የብድር ክምችት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ29 በመቶ በማሳደግ ወደ 25.5 ቢሊዮን ብር ማሳደግ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ባንኩ የቢዝነስ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ የሚያደርገው ጥረት እያደገ መምጣቱ እንደሆነ ተመላክቷል።አማራ ባንክ በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ26 በመቶ በማሳደግ ወደ 31.5 ቢሊዮን ብር አሳድጓል። ይህም ደንበኞቻችን በባንካችን ላይ እያሳደሩት ያለው እምነት እያደገ መምጣቱ እንደሚያሳይ ተገልጿል።የባንኩ አጠቃላይ ገቢ በ29 በመቶ በማሳደግ ወደ 5.6 ቢሊዮን ብር መጨመር መቻሉንም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ይፋ ያደረጉት።ሌላው አማራ ባንክ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው በዲጂታል ባንክ ሽግግር ለማድረግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራ ሲሆን፣ ይህም ተደራሽነትን በማስፋት አገልግለቱን የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ነው።የባንኩ ደንበኞችን ቁጥር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ 2.4 ሚሊዮን በማሳደግ ላይ መሆኑ በአገልግሎቱ መተማመን እና እርካታ እያደገ መምጣቱም ተመላክቷል።የሴቶችንና በአነስተኛ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አቅም ለማጎልበትም የዲጂታል ማይክሮ ብድር አገልግሎት 1.8 ቢሊዮን ብር ለ95,796 ደንበኞች መስጠት መቻሉን እና በዚህ ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ እንደሚሰራም ተገልጿል።ባንኩ እነዚህን ስኬቶች ሊያስመዘግብ የቻለው ባለፈው ዓመት የነበሩበትን ውስብስብ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችና ብልሹ አሰራሮች በተለይ፣ የደንበኞች የገንዘብ ክፍያ መስተጓጎልን በማስተካከሉ፣ያልተከፈለና እየጨመረ የሚሄድ የውጭ ምንዛሬ ዕዳ መፍትሄ መስጠት በመቻሉ፣ በከፍተኛ ደረጃ የተበላሸ የብድር ክምችት ለመቀነስ በትጋት በመስራቱ፣ ያስመዘግብ ከነበረው ከፍተኛ ኪሳራ ወጥቶ ወደ ትርፍ እንዲመጣ በመስራቱ፣ በርካታ ከባንኩ ብድር የወሰዱ ፕሮጀክቶች በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ያቆሙትን ሥራ እንዲቀጥሉ በማስቻሉ፣ ወደ ሌሎች ባንኮች የሄዱ በወጪ ንግድና በተለያዩ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ የባንኩ ደንበኞችን ለመመለስ በትኩረት መስራት መቻሉና ያጋጠመውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እጥረት መፍታቱ ባንኩ ላስመዘገበው ውጤት መሻሻል ምክንያት እንደሆነም ነው በጠቅላላ ጉባኤው መክፈቻ ወቅት የተገለፀው።
የጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ ማስታወቂያ ለአማራ ባንክ ባለአክሲዮኖች በሙሉ!
የጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ ማስታወቂያ ለአማራ ባንክ ባለአክሲዮኖች በሙሉ! የአማራ ባንክ አ.ማ የባለአክሲዮኖች 4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ቅዳሜ ኅዳር 20 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ስለሚካሄድ ባለአክሲዮኖች ወይም ህጋዊ ወኪሎቻቸው በጉባዔው ላይ እንድትገኙ ጥሪ እናስተላልፋለን፤ የጉባዔውን አጀንዳዎችንና ተጨማሪ መረጃዎችን እሁድ መስከረም 4 ቀን 2018 ዓ.ም በወጡት አዲስ ዘመን እና ሪፖርተር አማርኛ ዕትም ጋዜጦች ላይ ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡ ማሳሰቢያ ውድ ባለአክሲዮኖቻችን የባንካችን ጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔ መሟላት እንዲችል በዕለቱ በአካል መገኘት የማትችሉ በሚቀርባችሁ የባንካችን ቅርንጫፍ ወይም በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት በመገኘት ውክልና እንድትሰጡ እያሳሰብን ውክልና የምትሰጡት ሰው በጉባዔው ተገኝቶ ሊፈርምላችሁ የሚችል መሆኑን እንድታረጋግጡና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ SBB/91/2024 መሰረት ሁሉም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና የባንኩ ሠራተኞች በሙሉ ውክልና መቀበል የማይችሉ መሆኑን በአክብሮት እናሳውቃለን፡፡ የአማራ ባንክ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ! የአማራ ባንክ፣ከባንክ ባሻገር!
ኤኢትሬድ ግሩፕ እና አማራ ባንክ በአጋርነት በመስራት የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለማብቃት እና የዲጂታል የንግድ ልውውጥ በሶኮኩ አፍሪካ በኩል ለመፈፀም የሚያስችላቸውን ስራዎች በመስራት ላይ መሆናቸውን አስታወቁ።
ኤኢትሬድ ግሩፕ እና አማራ ባንክ በአጋርነት በመስራት የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለማብቃት እና የዲጂታል የንግድ ልውውጥ በሶኮኩ አፍሪካ በኩል ለመፈፀም የሚያስችላቸውን ስራዎች በመስራት ላይ መሆናቸውን አስታወቁ። ከሰሞኑ የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ንግድ ግሩፕ እና የአማራ ባንክ በኢትዮጵያ ዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን በሶኮኩ አፍሪካ ፕላትፎርም አማካኝነት ለማፋጠን ያቀደ አዲስ ጅምር በቅርቡ ይፋ አድርገዋል። በተለይ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ከኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የዲጂታል ንግድ አመቻች ሆነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ የሚያስችል ስልጠና መስጠት ጀምረዋል። የኤኢትሬድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉዓለም ሥዩም በዚህ ወቅት እንዳሉት ከ400 በላይ ወጣት ኢትዮጵያውያን የዲጂታል ንግድ አስተባባሪ ሆነው እንዲያገለግሉ ከሰሞኑ ስልጠናውን መስጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል። ይህ ፕሮግራም የክህሎት ማጎልበት ብቻ ሳይሆን ኑሮን ለማሻሻል፣ የስራ እድሎችን ለማስፋት እና ኢትዮጵያን በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስር እየተገነባ ባለው አዲስ አህጉራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ተሳታፊ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ጠቀሜታ በተለይ ኢትዮጵያ የቀጠናውን ነፃ ንግድ ያፀደቀች በመሆኑ ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታውን በማሳየት “በኢትዮጵያ የተመረቱ” ምርቶችን በመላው አፍሪካ በነፃነት እንዲገበያዩ የኤኢትሬድ ግሩፕ በሮችን ለመክፈት እንደሚያስችል የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ይህም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ውስን የውጭ ምንዛሪ ጥገኝነት በመቀነስ ተጨማሪ እሴትን ጨምረው የተመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ አዳዲስ መንገዶችን ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው አቶ ሙሉዓለም የገለፁት። የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ንግድ ግሩፕ በአፍሪካ ህብረት እና በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት በአህጉሪቱ ውስጥ የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን ለማበረታታት የተመሰረተ ድርጅት መሆኑን የገለፁት አቶ ሙሉ ዓለም ሥዩም ከአማራ ባንክ ጋር ያለው የስራ ግንኙነትም የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለስራ የሚያስፈልጋቸውን ፋይናንስ በማቅረብና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ምርታቸውን በሶኮኩ ፕላትፎርም አማካኝነት ለገበያ እንዲቀርቡ ማስቻል እንደሆነ እና ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት መሆኑንም አስታውቀዋል። የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው፣ በዚህ መርሃ ግብር ላይ ለተገኙ ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር ‹‹ይህ ትብብር ለሀገራችን ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ማብቃት የባንካችን ተልዕኮ ነው››። ‹‹እንደ አማራ ባንክ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እና በፈጠራ የታገዘ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት በገባነው ቁርጠኝነት በፅናት እንቀጥላለን›› ብለዋል። በስልጠናው ወቅት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የሶኮኩ አፍሪካ ፕላትፎርም በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚያመጣ ጠቅሰው በተለይ፡-የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ዕድገት በማጎልበት ለማኅበረሰቡ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር፤ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈጣሪዎች ትልቅ እንቅፋት ሆኖ የቆየውን የፋይናንስ ችግር የሚቀርፍ እና ተመጣጣኝ ፋይናንስ እንዲያገኙ የሚያስችል፤የሶኮኩ አፍሪካ የንግድ ሥራዎችን አስፈላጊ ከሆኑ የፋይናንስ አገልግሎቶች ጋር የሚያገናኝ፣ እንቅፋቶችን በመቅረፍ ሥራቸውን እንዲያሳድጉ የሚያግዝ፤የዲጂታል ግብይቶችን እና ፋይናንስን በማመቻቸት ዘርፉ ዘመናዊ የፋይናንስ አካታችነትን እና የንግድ እንቅስቃሴው በዘመናዊ መርህ ውስጥ እንዲያልፍ የሚያግዝ መሆኑን በመረዳቱ ነው ባንኩ አብሮ መስራት የወሰነው ብለዋል። የሥራ እና ክህሎት ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው ወጣቶች በኤኢትሬድ አፍሪካ ግሩፕና በአማራ ባንክ አማካኘነት የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን በሶኮኩ አፍሪካ አማካኝነት በኢትዮጵያ እንዲፋጠን እና የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን ተሳትፎ በሀገሪቱ በላቀ ደረጃ እንዲያድግ ድልድይ የሚሆኑ ሰልጣኞች የቀረበላቸውን እድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ እና በትኩረት በመስራት ለውጥ እንዲያመጡ አሳስበዋል። አማራ ባንክ እና የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ በጋራ በመሆን የኢትዮጵያን የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች (SMEs) ምርታቸውን እንዲሸጡና እንዲያስተዋውቁ የሚያስችል ስራዎችን ለመስራት በሂደት ላይ ይገኛሉ። ይህ ትብብር በኤ.ኢ.ትሬድ የፈጠራ ውጤት የሆነው ‹‹ሶኮኩ አፍሪካ›› የዲጂታል ፕላትፎርም አማካኝነት የሚከናወን ሲሆን፣ ከ200,000 በላይ ኢንተርፕራይዞችን በማሰልጠን፣ ወደ ምርት እንዲገቡና ከፍተኛ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ማገዝ እና የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ ነው። አማራ ባንክከባንክ ባሻገር!
አማራ ባንክ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር በልደታ ክፍለ ከተማ ስር የሚገኙ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ለነዋሪዎቹ አስረከበ፡፡
አማራ ባንክ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር በክፍለ ከተማው ስር የሚገኙ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ለነዋሪዎቹ አስረከበ፡፡ ባንኩ በክረምቱ ዝናብ ምክንያት ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ቤቶችን ከወረዳውና ከክፍለ ከተማው አስተዳደር ጋር ሆኖ በቅርበት ከለየ በኋላ እስከ 2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት ሰርቶ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራና የተቸገሩ አቅመ ደካማ ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ እንደሚያደርግ ቃል በገባው መሠረት ታድሰው የተጠናቀቁትን ቤቶች መስከረም 8 ቀን 2018 ዓ.ም ማስረከብ ችሏል። ባንኩ ገንብቶ ለአቅመ ደካሞች ያስረከባቸው ቤቶች ከባንክ አገልግሎት ባሻገር በህብረተሰቡ ዘላቂ ኑሮ መሻሻል ላይ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ ከባንክ ባሻገር የሚለውን መሪ ሃሳብ በተግባር ማሳያ እንደሆኑ የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ገልጸዋል። እንደ ባንክ የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ሥራዎች ላይ ተሳትፈን የራሱን አሻራ ማስቀመጥ አንዱ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ አማራ ባንክ እንደዚህ አይነት የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሲሠራ የመጀመሪያው እንዳልሆነ እና አሁንም ወደፊትም ማኅበረሰብን የማገዝ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ ቤቶቹ በፊት ከነበሩበት ለኑሮ የማይመቹ ከነበሩበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ፈርሰው እንደ አዲስ በመሰራታቸው ነዋሪዎቹ ተደስተው ማየታቸው የበለጠ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልጸው፣ ይህንን በጎ ተግባር አማራ ባንክ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲሠራ የሚያስፈልገውን ክትትል እና እገዛ በማድረግ ለፍፃሜ እንዲበቃ በማስቻሉ የልደታ ክፍለ ከተማን እና በአጭር ጊዜ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ በማድረግ ሂደት ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የልደታ ክ/ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው የማኅበረሰቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል በሚደረገው ሂደት አማራ ባንክ ተሳታፊ ሆኖ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ በመገኘቱ አመስግነው ባንኩ ሰው ተኮር ሥራዎችን እየሰራ በመገኘቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አያይዘውም ባንኩ እንደዚህ አይነት በጎ ተግባር ከልብ በመነጨ በጎ ፍላጎት በመነሳት ዝቅ ብሎ ታች ያለውን ማኅበረሰብ ለመርዳት ያደረገውን ተነሳሽነት አድንቀው ወደፊትም እንደዚህ አይነቱን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ አማራ ባንከ ቤቱን ሰርቶ ያስረከባቸው ነዋሪዎች በበኩላቸው ቀድሞ ይኖሩበት የነበረው ቤት ቆርቆሮው የተቀደደ በመሆኑ ዝናብ የሚያስገባ፣ግድግዳው የፈረሰ፣ ነፋስና ብርድ እየገባ በጤናቸው ላይ ጉዳት ያደርስባቸው እንደነበረ አስታውሰው አማራ ባንክ ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ በአጭር ጊዜ ሰርቶ ማስረከቡ ደስታ እንደፈጠረባቸውና እንዲህ ባማረ መልኩ በጥራት ገነንብቶ እና ለመኖር ምቹ አድርጎ ሶፋም ገዝቶ በአዲስ ዓመት አዲስ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ ማስቻሉ እንዳስደሰታቸው ገልፀው ልባዊ ምስጋናቸውን ለባንኩ አቅርበዋል። አማራ ባንክከባንክ ባሻገር!
የአማራ ባንክ የ2017 ዓ.ም. የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት አስጀመረ።
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ ነሐሴ 06 ቀን 2017 ዓ.ም አማራ ባንክ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር በክፍለ ከተማው ስር የሚገኙ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ለመኖሪያ ምቹ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታወቀ። ባንኩ በክረምቱ ዝናብ ምክንያት ለመኖር እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ቤቶችን ከወረዳውና ከክፍለ ከተማው አስተዳደር ጋር ሆኖ በቅርበት ከለየ በኋላ እስከ ዘመን መለወጫ ባሉት ቀናት ሰርቶ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራና የተቸገሩ አቅመ ደካማ ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ለማድረግ መታቀዱን በማስጀመሪያ መርሃ ግብር ወቅት ተገልጿል። ባንኩ ገንብቶ ለአቅመ ደካሞች የሚያስረክባቸው ቤቶች ከባንክ አገልግሎት ባሻገር በህብረተሰቡ ዘላቂ ኑሮ መሻሻል ላይ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ ከባንክ ባሻገር የሚለውን መሪ ሃሳብ በተግባር የሚያሳይበት እንደሆነ ነው የአማራ ባንክ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ የሆኑት አቶ እሸቴ የማታ በማስጀመሪያ መርሃ ግብር ወቅት ያስታወቁት።እኛ ከባንክ ባሻገር እንደሆንን እናምናለን ያሉት ተወካዩ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ ቤቶችን መገንባት ጠንካራ እና የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር መሰረታዊ ነገር በመሆኑ፣ እንደ አማራ ባንክ ይህ አይነቱ የማህበራዊ ኃላፊነት የመወጣት ተግባር ማህበረሰባችንን ከፍ ለማድረግ እና ለሁሉም ብሩህ የወደፊት ተስፋ ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።የቤት እድሳት ስራው በአጭር ጊዜያት ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአማራ ባንክ በልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ በተረከበው ቦታ የዋና መስሪያ ቤት ግንባታውን ለማስጀመር በዝግጅት ነው። ባንኩ አሁን በክፍለ ከተማው ተገኝቶ ያደረገው ድጋፍም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅርበት ችግሮችን እየፈታ ለመስራት ያለውን አቋም ማሳያ መሆኑን ነው በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ወቅት የክፍለ ከተማው የዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካይና የበጎ ፈቃድና የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ እንግዳው ጓዴ የገለጹት።የአማራ ባንክ ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ባሻገር ተደራሽነቱን በማስፋት ለማህበረሰብ ልማት ቁርጠኛ ሆኖ በመስራት ላይ ነው። በማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራት፣ ባንኩ ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በንቃት በመደገፍና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ አጋርነቱን ማሳየት፣ ለህብረሰተቡ ፋይዳ ያላቸው የአጭርና የረጅም ጊዜ ልማትን በሚያበረታቱ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ለህብረተሰቡ ያለውን ድጋፍ የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ ይህንን ድጋፍ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎችም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል። አማራ ባንክከባንክ ባሻገር!
አማራ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዲስትሪክቶች፣ የዋና መሥሪያ ቤት የሥራ ክፍሎች፣ ቅርንጫፎችና በግል የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሰራተኞች ዕውቅና እና ሽልማት አበረከተ።
አማራ ባንክ የ2024/25 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማና የ2025/26 በጀት ዓመታዊ የዕቅድ ውይይት የሥራ አመራሮች ጉባዔ ሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ሲያጠናቅቅ፣ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዲስትሪክቶች፣ የዋና መሥሪያ ቤት የሥራ ክፍሎች፣ ቅርንጫፎችና በግል የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሰራተኞች ዕውቅና እና ሽልማት አበርክቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ባንኩ ላስመዘገበው ውጤትና የባንኩን የ5 ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በመገምገም፤ በማጽደቅና የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማደረግ ባንኩ ከገባበት ጫና በማላቀቅ ሂደት የበኩላቸውን አመራር ሲሰጡ ለነበሩ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት ላደረጉት አስተዋፅዖ የባንኩን ሰራተኞች በመወከል የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ምስጋና አቅርበዋል፤ ዕውቅናም ሰጥተዋል፡፡ የባንኩ ሰራተኞች በዋና ሥራ አስፈፃሚው ለተደረገው አመራርና ሪፎርም ያዘጋጀውን ልዩ ምስጋናና ሽልማት በባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ደበበ አማካኝነት ለባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው አበርክቷል፡፡ በጉባዔው ማጠናቀቂያ ባለፈው በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ዲስትሪክቶች፣ የሥራ ክፍሎች፣ ቅርንጫፎች እና ግለሰቦችን ለማመስገን የዋንጫ፣ የምስክር ወረቀት እና የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ባንኩ ለዲስትሪክቶች፣ ለዋና መሥሪያ ቤት የሥራ ክፍሎች፣ ለቅርንጫፎችና በግል የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሰራተኞች ዕውቅና እና ሽልማት ያበረከተው በተለይ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣በብድር አሰባሰብ፣ የደንበኞች አገልግሎት፣ዲጅታል ባንኪንግ፣ ባንኩ በቀጣይ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ እና ሌሎች የአፈፃፀም መለኪያዎች ለሽልማት የተቀመጡ መስፈርቶች ነበሩ፡፡ የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ለተሸላሚዎች እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንዳሉት ይህ አይነቱ የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ ባንኩ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት መረባረብና ለላቀ ሥራ በመነሳሳት እንዲሰሩ ጠይቀው፣ በቀጣይ ሁሉም ለሽልማት እጩ መሆን ይገባዋል። የአማራ ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ደበበ በበኩላቸው፤ በአዲሱ በጀት ዓመት ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እና በዕቅዱ የተቀመጡ መለኪያዎችን ለማሳካት ሁሉም የባንኩ ሰራተኞች በጋራና በብርታት እንዲሰራና የባንኩን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ለማሳካት እንዲጥሩ ከአደራ ጋር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ባንኩ እንዲህ አይነት የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር ማዘጋጀቱ፣ የላቀ የአፈፃፀም ደረጃን መቀበልና እውቅና ለመስጠት፡ ልዩ አፈፃፀም፣ ትጋት እና ፈጠራ ላሳዩ ሰራተኞች እና የሥራ ክፍሎች እውቅና ለመስጠት እና ለማክበር፣ሌሎች ሰራተኞችና አመራሮች ለአማራ ባንክ ስኬትና ለላቀ ሥራ ለማነሳሳት፣ ለባንኩ ስኬት አስፈላጊ የሆኑትን እሴቶች እና መልካም ባህሪያት ለማጠናከር፣ ባንኩ ያስቀመጣቸውን ግቦች ማሳካት የሚያስችል መነሳሳት ለመፍጠር፣ በሰራተኛው መካከል ተባብሮ ለመሥራት ባህል ለመገንባት፣ የባለቤትነት ስሜትን የሚያጎለብት አዎንታዊ እና አመስጋኝ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር፣ ምስጋናን ለመግለጽና በባንኩ ውስጥ የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱት ያለውን ልባዊ ምስጋና ለማሳየት እንደሆነም በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።