አማራ ባንክ የብር 550.2 ሚሊዮን ትርፍ አስመዘገበ

Home / Announcements / አማራ ባንክ የብር 550.2 ሚሊዮን ትርፍ አስመዘገበ

አማራ ባንክ ከገቢ ግብር እና ከሌሎች የካፒታል ኢንቨስትመንቶች ያገኘው ገቢ ተጨምሮ ጠቅላላ ብር 550.2 ሚሊየን ትርፍ አስመዝግቧል፡፡

የባንኩ ባለአክሲዮኖች 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ ሚሊንየም አዳራሽ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን ያለፈው ዓመት የባንኩ የሥራ አፈፃፀም፣ የዚህ በጀት ዓመት ዕቅድና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የአማራ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ደበበ ሲሆኑ በንግግራቸውም ባለፈው በጀት ዓመት በባንክ ኢንዱስትሪው አዎንታዊና አሉታዊ ሁኔታዎችን የፈጠሩ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ክስተቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

ሰብሳቢው በንግግራቸው ባለፈው በጀት ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩት ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ያስከተሉት የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል በአገራችንም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳረፈ ሲሆን በተለይም የባንክ ሴክተሩን በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ተደማምረው አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ ገልጸዋል።

ባንኩ እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ ሥራ በጀመረበት ዓመት ከገጠመው ኪሳራ ተስፈንጥሮ በመውጣት ከግብር በኋላ ብር 524.5 ሚሊየን ትርፍ ማስመዝገቡን ለጉባዔው አብስረዋል። የቦርድ ሰብሳቢው አያይዘውም ባንኩ እ.ኤ.አ.  ሰኔ 30 ቀን 2024 ዓ.ም ላይ በድምሩ 25.1 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ በማሰባሰብ ከአቻ ተቋማት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ ባንኩ በጠቅላላው ብር 20.4 ቢሊየን ለዋና ዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዘርፎች በብድር መልኩ ማቅረቡን እንዲሁም በተለየ ሁኔታ ባቋቋመው የልማት ፋይናንስ መምሪያ አማካኝነት ዘመናዊ የእርሻ ትራክተሮች እና የግብርና ግብአቶች መግዣ የሚሆን ብድር ለአርሶ አደሩ ማመቻቸቱን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

አቶ ጋሻው ከተደራሽነት አንፃር በተደረገው ያልተቋረጠ ጥረት በበጀት ዓመቱ ተጨማሪ 43 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመላ ሀገሪቱ በመክፈት እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2024 ዓ.ም ላይ የቅርንጫፎቹን ብዛት ወደ 310 ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፣ ከዚህ በተጓዳኝ ቴክኖሎጂን አብዝተው ለሚጠቀሙ ደንበኞች አገልግሎቱን ምቹ ለማድረግ 130 ኤ.ቲ.ኤም ማሽኖችን ግብይት በሚበዛባቸው ቦታዎች በማስቀመጥ እንዲሁም ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ያካተተ የሞባይል ባንክ መተግበሪያ ማቅረብ እንደቻለ አውስተዋል። በዚህም የባንኩ ደንበኞች ብዛት ከ1.8 ሚሊዮን እንደደረሰ እና ከ570 ሺህ በላይ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ ደንበኞችን ማፍራት እንደተቻለ አሳውቀዋል።

የቦርድ ሰብሳቢው በንግግራቸው ባንኩን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማስቀመጥ እንዲቻል የዳሬክተሮች ቦርድ ባስተላለፈው ውሳኔ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌውን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድርጎ መሾሙን አስታወቀዋል፡፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ በዶ/ር ዮሐንስ አያሌው በሳልና ስትራቴጂያዊ አመራር ባንኩ ወደ ተሻለ ከፍታ እንደሚደርስ ሙሉ እምነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ባንኩ ለዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ መሥሪያ የሚሆን 10,579 ካ.ሜ ቦታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልደታ ክ/ከተማ የተረከበ መሆኑን እና አሁን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ብሎም ከቦታው ከሚነሱ ነዋሪዎች ጋር የካሳ ስምምነት በመፈጸም ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መደረሱን አብስረዋል፡፡

አዲሱ የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው የባንኩ አጠቃላይ የሃብት መጠን በ24 በመቶ በመጨመር አሁን ላይ 35.2 ቢሊየን ብር መድረሱን አስታውቀዋል። አያይዘውም የባንኩ አጠቃላይ ካፒታልና መጠባበቂያ ከነበረበት የ21 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ብር 7.1 ቢሊዮን እንደደረሰ እና ከዚህ ውስጥ የአክሲዮን ካፒታል 92 በመቶውን ወይም ብር 6.5 ቢሊዮን በመሆን ከፍተኛውን ድርሻ እንሚይዝ ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም ባንኩ ከዚህ በፊት የተስተዋሉትን የገበያ ተለዋዋጭነትን እና የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችን እንዲሁም የወደፊት የዕድገት አቅምን ከግምት ውስጥ በማስገባት የቀጣይ አምስት ዓመት (2025/26-2029/30) ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ ነድፎ ወደ እንቅስቃሴ እየገባ አስታውቀዋል። በአሰራር ልቀት እና ደንበኛን ያማከለ አገልግሎት ላይ ባንኩ ያለውን ቁርጠኝነት በዚህ ዓመት ዲጂታል ብድር እና የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎትን ጨምሮ አዳዲስ ምርቶችን በመልቀቅ፣ ተደራሽነትን በማስፋት እና የደንበኞችን ልምድ ከፍ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ እንደሚሠራ አስገንዝበዋል፡፡

Download ABa Mobile Banking

Download the app and join our digital world.

Copyright© 2024 Amhara Bank S.C. | All Rights Reserved

wpChatIcon
wpChatIcon